የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል (LLPIRDC) ቀደም ሲል የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት (LIDI) በመባል የሚታወቅ ሲሆን፤ ለኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪ የክህሎት ማሳደጊያ አገልግሎቶችን ለመስጠት በ1998 ዓ.ም በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ስር የተቋቋመ የመንግስት ተቋም ነው። ማዕከሉ ለቆዳና ለቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ የትምህርትና ስልጠና፣ የቴክኒክ አማካሪነት፣ የምርምርና ልማት እንዲሁም የላብራቶሪ ምርመራ አገልግሎቶችን ይሰጣል።
ማዕከሉ ለስልጠና እና ለቴክኒክ አገልግሎት አሰጣጥ የሚረዱ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የተሟሉላቸው ሞዴል ፋብሪካዎች (ሞዴል የቆዳ ማከሚያ፣ ሞዴል የጫማ ፋብሪካ፣ ሞዴል የቆዳ አልባሳትና የቆዳ ውጤቶች ፋብሪካ)፣ የሜካኒካል ወርክሾፕ እና የምርት ልማት ማዕከል አሉት። በተጨማሪም የምርት ጥራትና የአካባቢ ጥበቃ መስፈርቶችን ለመመርመር የሚያስችሉ ልዩ ልዩ የላብራቶሪ ተቋማት (የፊዚካል፣ የኬሚካል፣ የፍሳሽ ቆሻሻ እና የኢንስትሩሜንቴሽን ላብራቶሪዎች) አሉት።
የምርምር ማዕከሉ የራሱን ተቋማዊ አቅም ለማሳደግ እና የቆዳ ዘርፉን የአካባቢ ጥበቃ ተግዳሮቶች ለመቅረፍ የሚያስችሉ የጋራ ምርምሮችን ለማካሄድ፤ እንደ የህንድ ማዕከላዊ የቆዳ ምርምር ኢንስቲትዩት (CLRI)፣ የጫማ ዲዛይንና ልማት ኢንስቲትዩት (FDDI) እና የቻይና የቆዳና ጫማ ምርምር ኢንስቲትዩት (CLFI) ካሉ መሰል ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር ይሰራል::